Amharic Language, Literature and Folklore
Permanent URI for this collection
Browse
Browsing Amharic Language, Literature and Folklore by Subject "ስርዓተፆታዊ ዲስኩር ትንተና"
Now showing 1 - 1 of 1
Results Per Page
Sort Options
Item በከፍተኛ ትምህርት ተቋም መምህራን የሚታይ ስርዓተፆታዊ ዲስኩር ትንተና፤ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መነሻነት(አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ, 2006-05) ካሳው, ኂሩት; መሀመድ, ኑሩ (ዶክተር )የዚህ ጥናት ዋና ዓላማ በገላጭ ጥናት ደረጃ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በወንድና በሴት መምህራን በሚደረግ የስራ ላይ መስተጋብር የሚታየውን ተግባቦታዊ ስልት መግለፅ ሲሆን፤ በተግባራዊ ስነልሳን ጥናት ደረጃ ደግሞ ስርዓተፆታዊ የተግባቦት ስልት በስራ ቦታ ላይ የሚያስከትለውን የስርዓተ ፆታ ተባልጦን ማሳየት ነው፡፡ ስለሆነም የጥናቱ ትኩረት ሴቶችም ሆኑ ወንዶች በስራ ቦታ ላይ በሚያደርጉት ተግባቦታዊ መስተጋብር ሃሳባቸውንና ራሳቸውን እንዴት እንደሚገልጹ የንግግር አቀራረባቸውን በማየት የተናጋሪዎቹን የድስኩር ስልት መፈተሸ ነው፡፡ ጥናቱ የተፈተሸው በአገራችን ከሚገኙ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች መካከል በአመቺ ናሙናነት በተመረጠው በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ በሶስት ፋካሊቲዎች በሚያስተምሩ ሴትና ወንድ መምህራን ላይ ሲሆን፣ መምህራኑ በስራ ቦታቸው የስራ ጉዳይን አስመልክቶ ባካሄዱት መደበኛና ኢመደበኛ ተግባቦታዊ መስተጋብር ሃሳባቸውንና ራሳቸውን እንዴት እንደሚገልጹ በመመርመር ያተኮረ ነው፡፡ የጥናቱ መረጃ በዋናነት በአሳታፊ ምልከታ፤ በደጋፊነት ደግሞ በቡድን ተኮር ውይይት፣ በሰነድ ፍተሻና በመስክ ማስታወሻ የመረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያዎች አማካኝነት ተሰብስቧል፡፡ መረጃው የሂሳዊ ድስኩር ትንተና (Critical Discourse Analysis) ስልትን በመከተል ተተንትኗል፡፡ በዚህም መሰረት በጥናቱ ሁለቱም ፆታዎች በስራ ቦታቸው ላይ በሚደረጉ መደበኛና ኢመደበኛ ውይይቶች ላይ ሀሳባቸውን ከመግለጽ አንጻር ልዩነት ታይቷል፡፡ ይኸውም በመደበኛ ውይይት ላይ አብዛኛዎቹ ወንዶችና ከቁጥር የማይገቡ ጥቂት ሴቶች ሃሳባቸውን የሚገልጹ ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ ሴቶች ግን ሀሳባቸውን በስፋት ሲገልጹ አይታዩም፡፡ በሌላ በኩል ግን ሴቶች በበዙበት ኢመደበኛ ውይይት ላይ ሴቶች ሃሳባቸውን በመግለጽ ከፍተኛ ተሳትፎ ሲኖራቸው፤ በዚህ አውድ ደግሞ ወንዶች ሃሳባቸውን ከመግለጽ ይቆጠባሉ፡፡ ከዚህ በተለየ ሁኔታ ግን ሴቶች በበዙበት መደበኛ ውይይት ላይ ወንዶች ንቁ ተሳታፊና ሀሳባቸውን የሚገልጹ ሲሆን ሴቶች ግን ሃሳባቸውን አይገልጹም፡፡ ይህም ከፆታ የበላይነት ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ ሴቶች ኢመደበኛ እና የሴቶች ቁጥር የበዛበት ወይም ሴቶች ብቻ ያሉበት የውይይት አውድ ይመቻቸዋል የሚል አንድምታ አለው፡፡ የቋንቋ አጠቃቀምን በተመለከተ አብዛኛዎቹ ሴቶች በሀሳብ ልውውጥ ጊዜ ‹‹እህ›› እና ‹‹እሽ›› የሚሉ አጫጭር ድስኩራዊ ቃላትና ጥያቄያዊ ዓረፍተነገሮችን በመጠቀም ያልተሟላና ይልተብራራ ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ አብዛኛዎቹ ወንዶች ሀሳባቸውን ለመግለጽ አፅንኦታዊና ድምፀታዊ አገላለጾችን፣ ሴቶች ደግሞ ስነምግባራዊ አገላለጾችን ይጠቀማሉ፡፡ ወንዶች በእድሜም ሆነ በስራ ልምዳቸው ከፍ እያሉ ሲሄዱ ደግሞ ስነምግባራዊ ቃላትን መጠቀምን እንደሚመርጡ ጥናቱ አሳይቷል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ሴቶች በእድሜያቸውም ሆነ በስራ ልምዳቸው ከፍ እያሉ ሲሄዱ ሀሳባቸውንም ሆነ ራሳቸውን ለመግለጽ ደፋር እንደሚሆኑ ያመለክታል፡፡ ሴቶችም ሆኑ ወንዶች በተግባቦት ሂደት የሚያሳዩት ዲስኩራዊ ልማድን በተመለከተ በመደበኛ ውይይት ወቅት አብዛኛዎቹ ወንዶች ተራቸውን ሳይጠብቁ ድርሻ የመንጠቅ፣ የጣልቃ ገብነትና ተደርቦ የመናገር ድስኩራዊ ልማድ ሲኖራቸው፣ ሴቶች በበዙበት ኢመደበኛ ውይይት ላይ ግን ሴቶች ተራን ያለመጠበቅ፣ የንግግር ድርሻን ብቻ ሳይሆን የውይይት ርዕሰ ጉዳይንም የማስቀየር፣ ተደራርቦ የመናገር፣ የጎንዮሽ ወሬና ያለመደማመጥ ልማድ አላቸው፡፡ የጥናቱ ውጤት እንደሚያሳው አብዛኛዎቹ ወንዶች የሙያ ብቃታቸውንና እውቀታቸውን የውይይት መድረኮችን በመጠቀምና ያላቸውን ቅድመግንዛቤ በመጠቀም ይገልፃሉ፡፡ አብዛኛዎቹ ሴቶች ያላቸውን እውቀትና ሙያዊ ብቃት ሲገልጹ አይታዩም፡፡ በአጠቃላይ በተግባቦት ሂደት ሀሳብንም ሆነ ራስን በመግለፅ ሂደት ፍርሃት፣ ይሉኝታ፣ በራስ አለመተማመን፣ ድርሻ አለማግኘት፣ በጉዳዩ ላይ ቅድመ ግንዛቤ አለመኖር፣ የወንዶች በንግግር የበላይ መሆንና የስብሰባው ድባብ ከወንዶች ይልቅ ሴቶች እንዳይናገሩ ተፅዕኖ ከሚያደርጉባቸው ጉዳዮች በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን በምልከታ በተወሰደው መረጃ ከሁሉም በበለጠ ቅድመግንዛቤ አለመኖር፣ በራስ አለመተማመንና የንግግር ድርሻ አለማግኘት ዋናዎቹ ተፅዕኖዎች እንደሆኑና የዚህም ችግር ምንጭ ስርዓተፆታ እንደሆነ በጥናቱ ታይቷል፡፡ በመጨረሻም ችግሩን ለመቅረፍ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በስልጠናቸው ስርዓተፆታን መሰረት ያደረገ ‹‹የስራ ቦታ ተግባቦታዊ መስተጋብር ክህሎት›› ቢያካትቱ፣ እንዲሁም መሰል ጥናቶች በተለያዩ ከፍተኛ ተቋማት ቢካሄዱ ስርዓተፆታና ተቋማዊ ባህል በተግባቦታዊ መስተጋብር ላይ ያላቸውን ግንኙነት በማሳየት አስተዋፅዖ እንደሚኖረው ተጠቁሟል፡፡