የጠልሰም ባህላዊ ዕውቀትና መድኃኒትነት በፃታ ወረዳ
No Thumbnail Available
Date
2021-10
Authors
Journal Title
Journal ISSN
Volume Title
Publisher
Addis Ababa University
Abstract
ይህ ጥናት “የጠልሰም ባህላዊ ዕውቀትና መድኃኒትነት በጻታ ወረዳ” በሚል ርዕስ የቀረበ ሲሆን የጥናቱ
አነሳሽ ምክንያት የአካባቢውን ማህበረሰብ ባሕላዊ የህክምና እውቀት መመርመር ነው፡፡ የዚህ ጥናት ዋና
ዓላማ የጠልሰምን ባህላዊ እውቀት እና መድሀኒትነት ማሳየት ሲሆን የጠልሰም መስሪያ ግብዓቶችና
አዘገጃጀቱን ማብራራት፤ የጠልሰም ዓይነቶችን ለይቶ ማሳየት፤ በጠልሰም ላይ የሚሳሉ መንፈሳዊ ሥዕሎች
ለመድኃኒትነቱ ያላቸውን ፋይዳ ማሳየት፤ ለጠልሰም መስሪያ የሚሆን ቆዳ መረጣ ሥርዓተ ክዋኔን
ማብራራት፤ የሕመም መለያ መንገዶችን መጠቆም፤ ማህበረሰቡ ስለ እውቀቱ ያለውን አመለካከት
መመርመር እና መድኃኒት አዘጋጆቹን ወይም ጠልሳሚያኑ እውቀቱን ያገኙበትን ተስተላልፏዊ ሂደት
መመርመር ደግሞ የጥናቱ ንዑሳን ዓላማዎች ናቸው፡፡ እነዚህን ዓላማዎች ከግብ ለማድረስ የቃለ መጠይቅ
እና የመስክ ምልከታ መረጃ መሰብሰቢያ ዘዴዎች ጥቅም ላይ የዋሉ ሲሆን በእነዚህ መንገዶች የተሰበሰበው
መረጃም በፎቶ፣ በማስታወሻ መያዣ፣ በምስልና ድምጽ መቅረጫ መሳርያ እንዲሁም በመቅረጸ ድምጽ
መሳሪያ ተሰብስበው ተሰንደዋል፡፡ የመስክ መረጃ ሰጪዎች ዓላማ ተኮር የመረጣ ዘዴን መሰረት በማድረግ
የተመረጡ ሲሆን ከጠልሰም መድኃኒት ጠልሳሚያን፤ በጠልሰም መድኃኒት ሕክምና አግኝተው ከተፈወሱ
የመድኃኒቱ ተጠቃሚ ሰዎችና በመንደሩ አዋቂ ከሆኑ ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች እንዲሁም
ከቁልፍና አጋዥ የመረጃ ሰጪ አካላት የተሰበሰቡ መረጃዎች ተግባራዊና ክዋኔያዊ ንድፈ ሃሳቦችን መሰረት
በማድረግ በገላጭና ተንታኝ ስልት ተተንትነው ቀርበዋል፡፡ ጥናቱ በተመረጠው ፃታ ወረዳ ውስጥ ይህ
የጠልሰም እውቀት በስፋት ተተግባሪ የሚደረግባቸውን “ዳምትኩነ” እና “አርመር” የተባሉ ሁለት ቀበሌዎች
በናሙናነት የመረጠ ሲሆን በእነዚህ ቀበሌዎች በተደጋጋሚ የሚስተዋሉት ሕመሞችም ሾተላይ፣ ዓይነ ጥላ
(ሕጻናትን ገዳይ በሽታ)፣ ገርጋሪ፣ ደም መፍሰስ፣ ማዕሰረ አጋንንት፣ መግረሬ ጸር፣ ዛር መለመኛ ማውገዣና
ማስታረቂያ፣ መፍትሔ ስራይ እና መድፍነ ጸር መሆናቸው በጥናቱ ተረጋግጧል፡፡ ለእነዚህ ሕመሞች
በቁመት ልክ ከሚሰራ ቁም ክታብ፣ በወገብ እና በግንባር ከሚታሰር ጠልሰም በአንዱ መድኃኒቱ እንደሚሰጥና
መድኃኒት ከመስጠት በፊትም ዓይን በማየት አሊያም ዓውደነገስት ገልጦ ኮከብ በማንበብ ሕመም የመለየት
ተግባር እንደሚከወን በጥናቱ ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ እነዚህ ሕመሞች የየራሳቸው የሆነ ጸሎት ያላቸውና
እኩይ መንፈስ ማራቂያ አስማት ያሉበት እንደሆነም በጥናቱ ተስተውሏል፡፡ መናፍሰቱን ግዘፍ አስነስቶ
ሥዕላቸውን በመሳል ሕመምተኛው መናፍስቱን እንዳይፈራ የሚያደርግ ሥነ ልቡናዊ ሕክምና
እንደሚታከልበት ጥናቱ አረጋግጧል፡፡ ይህ እውቀት በቃል እና በጽሑፍ ሲተላለፍ የመጣ ቢሆንም አልፎ
አልፎ ጥበቡን እኩይ ለሆኑ ተግባራት የሚጠቀሙ ጠልሳሚዎች በመኖራቸው ማህበረሰቡ በተወሰነ ሁኔታ
ጥበቡን የመፍራት ጠልሳሚያንንም የመሸሽ ሁኔታ በመኖሩ ዕውቀቱ ለሀገር እና ለማህበረሰብ
የሚጠቅመውን ያህል ማደግ አለመቻሉን በጥናቱ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ሆኖም ይህ ጥበብ እኩይ
የማሕበረሰቡን ሕመም ከመፈወስ፤ ከመናፍስት ጋር የተያያዙ ሕመሞችን ከመፈወስ አንጻር ሀገራችን
ያላትን ጥበባዊ ዕውቀት የማሳየት ድርሻው የጎላ በመሆኑ ከወረዳው ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጀምሮ
የሚመለከታቸው አካላት እውቀቱን በማጎልበትና በማስተዋወቅ የራሳቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል፡፡
Description
Keywords
ባህላዊ ዕውቀትና መድኃኒትነት