የአርጐባ ብሄረሰብ የወሊድ፣ የጋብቻና የሀዘን ስነ ስርዓቶች ክዋኔ ትንተና፤ በአፋር ክልል፣ ዞን ሶስት፣ አርጐባ ልዩ ወረዳ

No Thumbnail Available

Date

2017-08-16

Journal Title

Journal ISSN

Volume Title

Publisher

Abstract

የፎክሎር አንድ ክፍል የሆነው ሀገረሰባዊ ልማድ ከሚይዛቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ስነ ስርዓት (Ritual) ነው፡፡ ከስነ ስርዓት ዓይነቶች መካከል ደግሞ የህይወት ሽግግር ስነ ስርዓቶች ይገኛሉ፡፡ ይህ ጥናት በህይወት ሽግግር ስነ ስርዓቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን "የአርጐባ ብሄረሰብ የወሊድ፣ የጋብቻና የሀዘን ስነ ስርዓቶች ክዋኔ ትንተና፤ በአፋር ክልል፣ ዞን ሶስት፣ አርጐባ ልዩ ወረዳ" በሚል ርዕስ የቀረበ ነው፡፡ የጥናቱ ዋና ዓላማ በአፋር ክልል ከሚኖረው የአርጐባ ብሄረሰብ የህይወት ሽግግር ስነ ስርዓቶች መካከል የወሊድ፣ የጋብቻና የሀዘን ስነ ስርዓቶችን ክዋኔ መተንተን ነው፡፡ በአፋር ክልል የሚኖረውን የአርጐባ ብሄረሰብ የወሊድ፣ የጋብቻና የሀዘን ስነ ስርዓቶች ለመተንተን የክዋኔ፣ መዋቅራዊ፣ ትዕምርታዊና ተግባራዊ ንድፈ ሀሳቦች ጥቅም ላይ የዋሉ ሲሆን የጥናቱን ዓላማ ለማሳካትና የምርምር ጥያቄዎችን ለመመለስ ካልዓይና ቀዳማይ መረጃዎች ተሰብስበዋል፡፡ ካልዓይ መረጃ ከጽሁፍ ሰነዶች፣ ቀዳማይ መረጃ ደግሞ የመስክ ስራ በማከናወን የተሰበሰበ ሲሆን በመስክ መረጃን ለመሰብሰብ ጥቅም ላይ የዋሉ ምልከታ፣ ቃለመጠይቅና ቡድን ተኮር ውይይት ዘዴዎች ናቸው፡፡ የጥናት ቦታና የመረጃ ሰጪ መረጣ የተከናወነው በአላማ ተኮርና በጠቋሚ የንሞና ዘዴ ነው፡፡ መረጃ የተሰበሰበባቸው አውዶች ተፈጥሯዊና አርቴፊሻል አውዶች ሲሆኑ መረጃው ከዓይነታዊ የመረጃ መተንተኛ ዘዴዎች ውስጥ ኢትኖግራፊ የጥናት ሞዴልን በመጠቀም ተተንትኗል፡፡ የሜታ ፎክሎር ምርመራም በመረጃ መተንተኛነት ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ የጥናቱ ግኝት እንደሚያሳየው በአፋር ክልል የሚኖረው የአርጐባ ብሄረሰብ የጋብቻ ስነ ስርዓት ክዋኔ መዋቅር በቅድመ መለየት፣ መለየት፣ ሽግግርና መቀላቀል ደረጃዎች ሊከፈል የሚችል ሲሆን የወሊድና የሀዘን ስነ ስርዓቶች ክዋኔዎች ደግሞ በመለየት፣ ሽግግርና መቀላቀል ደረጃዎች ሊከፈሉ የሚችሉ ናቸው፡፡ በብሄረሰቡ የወሊድ ስነ ስርዓት ክዋኔ ስነቃል (ዱዓዎች፣ ዝኪሮች)፣ ቁሳዊ ባህል (ሽታ፣ አዝጋሮ፣ ወይባ፣ አልባሳት) እና ሀገረሰባዊ ልማድ (እምነቶች፣ ባህላዊ ሕክምና፣ ጭስ መሞቅ) ፎክሎሮች ተለይተዋል፡፡ በጋብቻ ስነ ስርዓት ክዋኔ ስነቃል (ቃል ማሰሪያዎች፣ መወከያዎች፣ ዱዓዎች)፣ ቁሳዊ ባህል (ወይደል፣ ምግብና መጠጥ፣ አልባሳት፣ ጌጣጌጥ፣ ጉፍታ)፣ ሀገረሰባዊ ልማድ (እምነቶች፣ ጭስ መሞቅ) እና ሀገረሰባዊ ትውን ጥበባት (ሺሎ፣ ዘፈኖች) ፎክሎሮች ተለይተዋል፡፡ በሀዘን ስነ ስርዓት ክዋኔም ስነቃል (ዱዓ፣ ማጽናኛዎች፣ መሰናበቻዎች)፣ ቁሳዊ ባህል (ምግብና መጠጥ፣ የከፈን ጨርቅ፣ ማግ፣ መዋስ) እና ሀገረሰባዊ ልማድ (ባህላዊ ህክምና፣ እምነት) ፎክሎሮች ተለይተዋል፡፡ በብሄረሰቡ በወሊድ ስነ ስርዓት ክዋኔ ውስጥ ያሉ ቃላዊ (የዱዓ ቃላት)፣ ቁሳዊና (ማር) ድርጊታዊ (ጣትን በገበታ ዙሪያ ማድረግ፣ ገበታን ከፍ ማድረግ፣ ድፍን ቅል አልጋ ላይ ማድረግ)፣ በጋብቻ ስነ ስርዓት ክዋኔ ውስጥ ያሉ ቃላዊ (የዱዓ ቃላት)፣ ቁሳዊ (የወይደል ቀለም፣ ጉፍታ) እና ድርጊታዊ (ለሙሽራ ጉፍታ የምትጭን ሴት አግብታ ያልፈታች መሆኗ) እና በሀዘን ስነ ስርዓት ክዋኔ ውስጥ ያሉ ድርጊታዊና (ጥልፍ መተርተር፣ ውሀ ማርከፍከፍና እርጥብ ቅጠል መጐዝጐዝ፣ መዋስን በጠዋት ውሀ አርከፍክፎ ማጠፍ፣ እጅንና ፊትን በቀዝቃዛ ውሃ መታጠብ) ቁሳዊ (ውሀ፣ መዋስ) ትዕምርቶች ተለይተዋል፡፡ የብሄረሰቡ የወሊድ ስነ ስርዓት ማህበራዊና (ወላድ መንከባከብ፣ አራስ መጠየቅ) ስነ ልቡናዊ (ባህላዊ ህክምናና የአምሮት ስነ ስርዓት) ፋይዳዎች አሉት፡፡ የብሄረሰቡ የጋብቻ ስነ ስርዓት የአሻጋሪነት (ትዳር የሌለውን ሰው ወደ ባለትዳርነት)፣ ማህበራዊ (ሰዎችን በአንድ ያገናኛል)፣ ኢኮኖሚያዊ (ስጦታዎች)፣ ስነ ልቡናዊና (ዱዓና ባዷሼህ) የተግባቦትና የማዝናናት (ዘፈኖች) ፋይዳዎች አሉት፡፡ የብሄረሰቡ የሀዘን ስነ ስርዓት ተግባቦታዊና ማህበራዊ (ለቅሶ መድረስ)፣ ኢኰኖሚያዊና (ሀፈሻ) ስነ ልቡናዊ (በጋራ ማልቀስና ሶደቃ) ፋይዳዎች አሉት፡፡ ለውጥን ተቋቁመው የቀጠሉ ክዋኔዎች ቢኖሩም በብሄረሰቡ የወሊድና የሀዘን ስነ ስርዓቶች ላይ የክዋኔ ለውጦች፤ በብሄረሰቡ የጋብቻ ስነ ስርዓት ላይ ደግሞ የክዋኔና የመዋቅር ለውጦች ታይተዋል፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮች ተለይተው የሜታ ፎክሎር ምርመራም ተደርጐባቸዋል፡፡ በጋቸኔ ጤና ጣቢያ የተሰራው ባህላዊ ጐጆ ለታሰበለት ዓላማ ቢውል፣ የነፍሰጡር የምግብ ክልክሎችና ከነፍሰጡሯ ጤና አንፃር ጉዳት ያለው መሆኑና አለመሆኑ ቢጠና፣ በወሊድ ጊዜ የሚከወኑ አንዳንድ ክዋኔዎች ለምሳሌ፣ መነቅነቅ የሚያስከትሏቸው የጤና ጉዳቶች ካሉ በጥናት ቢለዩ፣ ሀፈሻን ከዘመናዊ የመረዳጃ ተቋማት ጋር ማስተሳሰር ቢቻል፣ ዚያራ በዝርዝር ቢጠና ጥሩ ነው፡፡

Description

Keywords

Citation