በደላንታ ወረዳ የአበሹቴ እና የኧኸይቦሌ ቃል ግጥሞች ክዋኔና ይዘት ትንተና

No Thumbnail Available

Date

2007-06

Journal Title

Journal ISSN

Volume Title

Publisher

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ

Abstract

የዚህ ጥናት ዋና ዋና ትኩረቶች ሁለት ናቸው። አንደኛው የትኩረት ነጥብ በደላንታ ወረዳ የአበሹቴ እና የኧኸይቦሌ ቃል ግጥሞች እንዴትና መቼ እንደሚከወኑ ማሳየት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ይዘታቸውን መተንተን ነው። ቃል ግጥሞቹ በሚከወኑበት ቦታና ጊዜ በመገኘት ለዚህ ጥናት የሚጠቅሙ መረጃዎች ተሰብስበዋል። መረጃዎቹ የተሰበሰቡት በምልከታና በቃለ መጠይቅ ነው። በምልከታና በቃለ መጠይቅ ወቅት የተገኙ መረጃዎችን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግና የተሟላ መረጃ ለማግኘት የቡድን ውይይት ተደርጓል። ጥናቱ የሰባት በዓላትን የቃል ግጥሞች ክዋኔ ተመልክቷል። የአበሹቴ እና የኧኸይቦሌ ቃል ግጥሞች መከወኛ አጋጣሚ ክብረ በዓላት ናቸው። በጥናቱ ህዳር 21 ቀን የማሪያም ታቦትን ንግሥ አስመልክቶ የአበሹቴ እና የኧኸይቦሌ ጨዋታዎች እንደሚጀምሩና እስከ ፋሲካ በዓል ድረስ በሚከበሩ ዓውደ ዓመቶችና የንግስ በዓላት እንደሚቀጥሉ ተረጋግጧል። ቃል ግጥሞቹ በፆታ ልዩነት ላይ ተመሥርተው የሚገጠሙ ናቸው። የአበሹቴ ቃል ግጥሞች ሴቶችን ብቻ ለማወደስና ለመሳደብ የሚገጠሙ ሲሆን የኧኸይቦሌ ቃል ግጥሞች ደግሞ ሴቶችን በማወደስ ብቻ ሲያልፏቸው በአብዛኛው ወንዶችን የሚሳደቡ በጥቂቱ የሚያሞግሱ ናቸው። በሁለቱ ቃል ግጥሞች መካከል የአከዋወን ሂደት ልዩነትም እንዳለ ጥናቱ አሳይቷል። የአበሹቴና የኧኸይቦሌ የቃል ግጥሞች አከዋወን የተለያየ ቢሆንም የሁለቱም ቃል ግጥሞች አጠቃላይ ይዘት የደላንታ ወረዳን ህብረተሰብ ባህል መጠበቅና ማንነቱን ማንጸባረቅ መሆኑን ጥናቱ አመላክቷል። ጥናቱ የቃል ግጥሞቹ የሚከወኑባቸው አጋጣሚዎች ድግግሞሽ እየጨመረ መምጣቱን ያሳያል። ለዘመናት በዓመት አንድ ጊዜ በፋሲካ በዓል ብቻ ይከወኑ የነበሩት እነዚህ ቃል ግጥሞች አንድ ትውልድ ሳያልፍ በአንድ ቀበሌ ውስጥ በዓመት ከስድስት ጊዜ በላይ በመከወን ላይ መሆናቸውን ጥናቱ ያስረዳል። በገና፣ በጥምቀት እና በፋሲካ በዓላት ጨዋታዎቹ በሚከወኑባቸው ሁሉም ቀበሌዎች ቃል ግጥሞቹ የሚከወኑ ሲሆን በንግስ በዓላት ግን በተወሰኑ የታቦት ንግስ ባለባቸው ቀበሌዎች ብቻ የሚከወኑ መሆኑን በጥናቱ ተረጋግጧል። ከክዋኔው ጋር ተያይዞ ድግግሞሹ (የሚከወኑበት አጋጣሚ) የጨመረ ቢሆንም በከተማ እና በከተማ ዙሪያ በሚገኙ ቅርብ ቀበሌዎች ጨዋታዎቹ እየቀሩ መሆኑን ከጥናቱ መረዳት ተችሏል።

Description

Keywords

የኧኸይቦሌ ቃል ግጥሞች

Citation