የመርሐ ቤቴ ልጃገረዶች የፋሲካ ጨዋታ ክዋኔ እና ፋይዳ

No Thumbnail Available

Date

2023-11

Journal Title

Journal ISSN

Volume Title

Publisher

አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ

Abstract

ይህ ጥናት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በሰሜን ሸዋ ዞን፣ በመርሐ ቤቴ ወረዳ የፋሲካ በዓልን መሰረት በማድረግ በሚከበረው የልጃገረዶች ባህላዊ የፋሲካ ጨዋታ ክዋኔ እና ፋይዳ ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን ይህን ጥናት ለመስራት ምክንያት ከሆኑት ምክንያቶች መካከል አንደኛ የመርሐ ቤቴ ልጃገረዶች የፋሲካ ጨዋታ እየደረሰበት ካለው የመደብዘዝና የመጥፋት ስጋት ለመታደግ የየጨዋታዎቹን ክዋኔና ፋይዳ ሰንዶ የማቆየት ፍላጎት ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ባደረግሁት የቀደምት ጥናቶች ዳሰሳ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ የተሰሩ ጥናቶች ባለማግኘቴ ይህን ክፍተት ለመሙላት በማሰብ ነው፡፡ የጥናቱ ዋና ዓላማ “የመርሐ ቤቴ ልጃገረዶች የፋሲካ ጨዋታን አከዋወንና ፋይዳ መመርመር” ነው፡፡ ይህን ዓላማ ከግብ ለማድረስ በወረዳው የሚከወነው የልጃገረዶች የፋሲካ ጨዋታ ታሪካዊ አጀማመር መነሻ ምክንያቶች ምን ምን ናቸው? ስንት አይነት አና ምን ምን ዓይነት ጨዋታዎች ይከወናሉ? በወረዳው የሚከወነው የፋሲካ ጨዋታ ክዋኔ ሂደት ምን ይመስላል? የፋሲካ ጨዋታ ለተጠኝው ማህበረሰብ ምን ፋይዳ አለው? በጨዋታዎቹ ክወኔ ቀጣይነትና ይዘት ላይ ምን ዓይነት ስጋቶች ይስተዋላሉ? የሚሉ መሰረታዊ የምርምር ጥያቄዎች ተዘጋጅተው ምላሽ አግኝተዋል። ጥያቄዎቹን ለመመለስና የጥናቱን ዓላማ ለማሳካት የመርሐ ቤቴ ወረዳን ይወክላሉ ተብለው ከተመረጡት ከዓለም ከተማ፣ ከአፈዘዝ በርቃቶ፣ ከግሬት ወቸዋርኝ፣ ከአገሪት ቁምአምባ እና ሰባጌ ሃሮገንዳ ቀበሌዎች ስለጨዋታው ታሪክ ያውቃሉ ከተባሉ የሃገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ተጫውተው ካሳለፉ እናቶች፣ ከጨዋታው ተሳታፊ ልጃገረዶችና ወጣት ወንዶች እና ከባህልና ቱሪዝም ባለሙያዎች በአጠቃላይ ከአርባ አራት መረጃ አቀባዮች በምልከታ፣ በቃለ መጠይቅና በተተኳሪ የቡድን ውይይት መረጃዎች ተሰብስበዋል፡፡ የጥናቱን ቦታ እና መረጃ ሰጭዎች ለመምረጥ የዓላማ ተኮር የናሙና አመራረጥ ዘዴ ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን መቅረፀ ድምፅ፣ የእጅ ስልክ፣ የቪዲዮና ፎቶ ካሜራና ማስታወሻ ደብተር መረጃ ለመሰብሰብ ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡ ከጥናቱ ጋር ተዛማጅነት ያላቸውና ጥናቱ የተነሳበትን ዋና ጉዳይ የሚያጠናክሩ ማጣቀሻዎች፣ ዋቢ ጽሑፎች፣ ቀደምት ተዛማጅ ጥናቶች ካዕላይ የመረጃ ምንጮች ከአብያተ መጻሕፍና ከኤሌክትሮኒክስ የመረጃ መረብ በንባብ ተቃኝተዋል፡፡ በዚህ መሰረት ስለርእሰ ጉዳዩ አስረጅ የሆኑ ጽንሰ ሃሳቦችና ቀደምት ጥናቶች ተዳስሰዋል፡፡ ጥናቱ አይነታዊ እንደመሆኑ መጠን በምልከታና በቃለ መጠይቅ የተሰበሰበው መረጃ በአግባቡ ተደራጅቶ ገላጭ የትንተና ዘዴን በመጠቀም ተተንትኗል፡፡ ለመረጃ ትንተና የክዋኔያዊና ተግባራዊ ንድፈ ሃሳቦች አገልግለዋል፡፡ የመርሐ ቤቴ ልጃገረዶች የፋሲካ ጨዋታ ታሪካዊ ዳራው/መነሻው/ የክርስትና ሃይማኖት እንደሆነና ከትንሳኤ እስከ ዳግም ትንሳኤ ድረስ አንድ ሳምንት በሚቆየው በዚህ ሁነት ልጃገረዶች ቀደም ብለው በሁለት መንገድ ቅድም ዝግጅት በማድረግ ከጫና ነጻ ሆነው በጨዋታው ላይ እንደሚሳተፉ እና አስር ዓይነት ጨዋታዎች ባህሉ የሚፈቅደውን ህግ በመከተል በቡድን እንደሚከውኑ ጥናቱ አሳይቷል፡፡ ጨዋታው ማህበራዊ መስተጋብርን በማጠናከር፣ ባህልና ሃይማኖትን በማስቀጠል፣ ወጣቶች በባህላቸውና በማንነታቸው እንዲኮሩ በማድረግ፣ አካላዊና ሥነልቡናዊ ጥንካሬአቸውን በማዳበር፣ በራስ መተማመናቸውን በማጎልበትና ሃሳባቸውን በነጻነት እንዲገልጹ በማድረግ በኩል ከፍተኛ ማህበራዊ፣ ሥነለቡናዊና አካላዊ ፋይዳዎች ቢኖሩትም በውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ምክንያት ስጋት እንደተጋረጠበት የጥናቱ ውጤት አመላክቷል፡፡ ከዚህ በመነሳትም የአካባቢው ማህበረሰብና የሚመለከታቸው አካላት የጨዋታውን ፋይዳ በመገንዘብ ሃላፊነታቸውን ቢወጡ፤ በማህበራዊ፣ ሥነ ለልቡናዊና ስፖርታዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ተቋማትና የመስኩ ምሁራን ከዚህ ጥናት በበለጠ ሰፊ ጊዜና በጀት መድበው በእያንዳንዱ ጨዋታ የሚታዩ ጉዳዮችን አጥንተው የሚያበረክተውን ፋይዳ ቢያሳውቁ፤ ጨዋታው እንዲታወቅና ጎብኝዎች እንዲኖሩት ለማድረግ ባህልና ቱሪዝም፣ መገናኛ ብዙኀንና የሚመለከታቸው የመንግስትና የግል ተቋማት ትኩረት ሰጥተው በጋራ ቢሰሩ የሚሉ የይሁንታ ሃሳቦች ተጠቁመዋል፡፡

Description

Keywords

Citation