የኮንሶ ብሔረሰብ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓት
No Thumbnail Available
Date
2006-06
Authors
Journal Title
Journal ISSN
Volume Title
Publisher
አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ
Abstract
የዚህ ጥናት ትኩረት በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በኮንሶ ብሔረሰብ የሚከናወን ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓትን በመመርመር የግጭት መፍቻ ተቋማት በማህበረሰቡ ውስጥ የሚኖራቸውን ሚና እና ስርዓቱ ምን እንደሚመስል በመተንተን በስርዓቱ ወቅት የሚነገሩ አባባሎችና ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንዲሁም ልዩ ልዩ ትዕምርቶችን በመለየት የስርዓቱን ፋይዳ ማሳወቅ ነው፡፡ ይህንንም ለማሳካት በቅድሚያ በዘርፉ ስለብሔረሰቡና ስለ አካባቢው የተጻፉ የተለያዩ ጽሑፎችን በማንበብና መነሻ ሀሳብ ይዞ ወደ መስክ በመሄድ በቃለመጠይቅ (መደበኛና ኢ-መደበኛ)፣ በአካል ምልከታ እንዲሁም፤ የውስን አትኩሮት ቡድን ውይይት መረጃ የተሰበሰበ ሲሆን፣ መረጃው በሚሰበሰብበት ወቅት መቅረፀ ድምጽና ምስል ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ መረጃው የተሰበሰበው በኮንሶ ወረዳ በካራት አገልግሎት ስር ባሉ ሶስት ቀበሌዎች ሲሆን፣ ሽማግሌዎች፣ የጎሳ መሪ፣ ሴቶችና የወጣት ቡድን ተወካይ እንዲሁም ከፍትህ አካላት በጠቅላላ 16 ሰዎች በመረጃ አቀባይነት ተሳትፈዋል፡፡ የተሰበሰበው መረጃ ገላጭ ዘዴን በመጠቀም ተተንትኗል፡፡
በብሔረሰቡ ከቀላል እስከ ከባድ ግጭቶችን በመፍታት ዘላቂ ሰላም የሚያሰፍኑበት በየደረጃው የሚከናወን ሶስት ባህላዊ የዳኝነት መዋቅር እንዳላቸው ጥናቱ ያሳያል፡፡ ከሶስቱ ባህላዊ የዳኝነት መዋቅርና አደረጃጀት በላይ የሆኑ ጉዳዮች ወደ “ኻኻ” ወይም መሀላ ተመርተው የመጨረሻ ዕልባት እንደሚያገኙ ጥናቱ ይጠቁማል፡፡ በዕርቅ ድርድሩ ወቅት ለስርዓቱ የሰመረ አካሄድ በሽማግሌዎች የሚነሱ የተለያዩ አባባሎች፣ ምሳሌያዊ አነጋገሮች፣ ምርቃቶችና ምስጋናዎች ትልቅ መሳሪያ መሆናቸውን ጥናቱ አሳይቷል፡፡
በብሄረሰቡ ባህላዊውና መደበኛው የፍትህ ስርዓት የግጭት አፈታት ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ የሚሰሩበት አሰራርና ቅብብሎሽ መኖሩ ለባህላዊው የፍትህ ስርዓቱ ዘላቂነት የጎላ ድርሻ እንዳለው ጥናቱ ይጠቁማል፡፡ ባህላዊ የፍትህ ስርዓቱ ዋነኛ የፍትህ ተቋም ሆኖ የዘለቀ ቢሆንም፣ የማህበረሰቡን አቅም ያላገናዘበ ቅጣት የሚጣልበት ሁኔታ መኖሩና አወሳሰኑ ወጥነት የሌለው መሆኑ የስርዓቱ ክፍተት እንደሆነ ጥናቱ ያመለክታል፡፡
ሽማግሌዎች ጠበኞችን በማስታረቅ ሂደት ደረቅ ማሽላ አኝከው በመትፋት፣ ጠበኞችም በዕርቅ ስርዓቱ አንድ ስለመሆናቸው ለማረጋገጥ በአንድ ቅል በጋራ ባህላዊ መጠጥ (ጨቃ) በመጠጣት እንዲሁም እንደወንጀሉ ክብደት ከሚፈጽሙት ዕርቅ በኋላ አካባቢውን በደም፣ በፈርስና በቅዱስ ውኃ በመርጨትና በመታጠብ (የማንጻት ስራ) ዕርቁን እንደሚያፀኑ ጥናቱ ያሳያል፡፡
Description
Keywords
የኮንሶ ብሔረሰብ ባህላዊ የግጭት