የዳባት ወረዳ ገበሬዎች የስራ ቃል ግጥሞች ክዋኔና ማህበራዊ ህይወታቸው

No Thumbnail Available

Date

2006-06

Journal Title

Journal ISSN

Volume Title

Publisher

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ

Abstract

ከዚህ በፊት በመጀመሪያም ሆነ ሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ በዳባት ወረዳ ገበሬዎች ቃል-ግጥም ክዋኔና ማህበራዊ ህይወት ላይ ጥናት አልተደረገም፡፡ በገበሬዎች ቃል ግጥም ላይ የተለያዩ አጥኝዎች በተለያዬ ቦታ ጥናት ቢያደርጉም ቃል ግጥም ከቦታ ቦታ፣ ከከዋኝ ከዋኝ ሊለያይ የሚችል በመሆኑና የገበሬዎች ማህበራዊ ህይወትና የዕለት ተዕለት ውሎ ምን እንደሚመስል መገለፅ አለበት በሚል እምነት ይህ ጥናት የዳባት ወረዳ ገበሬዎች ቃል ግጥም ክዋኔና ማህበራዊ ህይወት ላይ የተደረገ ነው፡፡ የጥናቱ ዋና ዓላማ የዳባት ወረዳ ገበሬዎች በተለያዩ የስራ አይነቶች(አጋጣሚዎች) ስራቸውን በሚያከናውኑበት ወቅት የሚያዜሟቸውን ቃል ግጥሞች በአውዳቸው በመሰብሰብ የሚያነሷቸውን ርዕሰ ጉዳዮች መተንተን፣ የግጥሞቹን ማህበራዊ ፋይዳ መግለፅና ገበሬዎች ያላቸውን ማህበራዊ ግንኙነትና የዕለት ተዕለት ውሎ ማሳየት ነው፡፡ ጥናቱ በዋናነት በክዋኔ ተኮር ንድፈ ሀሳብ የተቀነበበ ሲሆን እንደአስፈላጊነቱም በተግባራዊ ንድፈ ሀሳብ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ የጥናቱ አቀራረብ በገላጭ የምርምር ዘዴና ይዘት ትንተና ላይ ተመስርቷል፡፡ ለጥናቱ ግብዓት የሚሆኑ መረጃዎችም ከቀዳማይና ካልዓይ የመረጃ ምንጮች ተሰብስበዋል፡፡ ቀዳማይ መረጃዎችም በምልከታና ቃለ መጠይቅ ዘዴዎች የተሰበሰቡ ሲሆን እንደአስፈላጊነታቸውና እንደ መረጃ ሰጭዎቹ ፍላጎት በቪዲዮ ካሜራ፣ በፎቶ ካሜራ፣ በመቅረፀ ድምፅና በማስታወሻ ደብተር ተሰንደዋል፡፡ ጥናቱ ከወረዳዋ 30 ቀበሌዎች መካከል በተመረጡ ሰባት ቀበሌዎች ላይ የተደረገ ሲሆን መረጃዎችም ከ33 ቁልፍና ከ15 ረዳት መረጃ አቀባዮች ተሰብስበዋል፡፡ የተሰበሰቡት በውቂያ፣ በአጨዳ፣ በእርሻ፣ በአረምና በጉልጓሎ የስራ አጋጣሚዎች በአውድ ውስጥና ከአውድ ውጭ ሲሆን ከ580 በላይ ቃል ግጥሞች ተሰብስበዋል፡፡ ከተሰበሰቡት ቃል ግጥሞች ገበሬዎች በተደጋጋሚ ያነሷቸው 54 ቃል ግጥሞች ተመርጠው በተከወኑበት አውድ መሰረት በሚያነሱት ርዕሰ ጉዳይ ተከፋፍለው ገለፃና የይዘት ትንተና ተደርጎባቸዋል፡፡ ከመረጃ ትንተናው ግኝት መረዳት እንደሚቻለው የዳባት ወረዳ የኦርቶዶክስና እስልምና እምነት ተከታይ ገበሬዎች ጥብቅ ግንኙነት የሚፈጥሩት በጋብቻ፣ በተዝካር፣ ix በዓመታዊ ክብረ በዓላት፣ በሰንበቴ፣ በለቅሶ፣ በክርስትና፣ አበልጅነትና በሆበራ ስራ ጊዜ መሆናቸው በጥናቱ ተገልጿል፡፡ የእስልምና እምነት ተከታዮች በእምነታቸው የማይፈቀደውን በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ከባድ ከባድ የሚባሉትን የቅዱስ ሚካኤል፣ ማሪያም፣ ባለእግዚያብሄርና ሰንበት (እሁድ) በዓላትን ያከብራሉ፡፡ የሚያከብሩበትም ምክንያት የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ገበሬዎች አዝዕርታቸውን በረዶ ሲደበድበውና አንዳንድ ችግሮች ሲያጋጥሟቸው የችግሩ መንስኤ አድርገው ስለሚቆጥሯቸው ከአገር ባህል ሳይወጡ ግንኙነታቸውን በማጠናከር ተቻችለው በሰላም ለመኖር መሆኑን ጥናቱ ያሳያል፡፡ እነዚህ ገበሬዎች በአዘቦት ቀን፣ በሰንበት ቀን (እሁድና ቅዳሜ)፣ በዓመታዊ ክብረ በዓላት ቀንና በመንግስት በዓላት ቀን የተለያዩ ተግባራትን ያከናውናሉ፡፡ የስራ ድርሻቸውንም ስንመለከት ሴቶች ከቤት ስራቸው በተጨማሪ የውጭ የግብርና ስራ በማከናወን ሰፊውን ቦታ ሲይዙ ወንዶች በመስክ ስራ ብቻ ስለሚሳተፉ በሴቶች ላይ የስራ ጫና እንደሚፈጠርባቸው ጥናቱ ይጠቁማል፡፡ የዳባት ወረዳ ገበሬዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች ከቤተሰቦቻቸውና ጓደኞቻቸው የሰሙትን ቃል ግጥም ከነዜማ አወራረዱ በመሸምደድ፣ የራሳቸውን ፈጠራ በመጠቀምና አውድን መሰረት አድርገው የቃል፣ የሀረግ፣ የስንኝና የይዘት ለውጥ በማድረግ፣ ለውጥ ሳያደርጉና ሙሉ ለውጥ በማድረግ ይከውናሉ፡፡ አብዛኛውን ጊዜም በሽምደዳ እንደሚያቀርቡና የሚከውኑትም በተናጠል፣ በጥንድና በቡድን ስልት እንደሆነ በጥናቱ ታይቷል፡፡ ገበሬዎች በእርሻ፣ በውቂያ፣ በአጨዳ፣ በአረምና በጉልጓሎ የስራ አጋጣሚዎች ባዜሟቸው ቃል ግጥሞች ብሶትና ምሬትን፣ ትችትን (ስድብ)፣ ውዳሴን፣ ምክርን፣ የወንድምን አስፈላጊነት ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም ስለበሬ፣ ስለፍቅር፣ ስለተስፋና ስለፀፀት የሚያወሱ ርዕሰ ጉዳዮችን አንስተዋል፡፡ ገበሬዎች ቃል ግጥሞቹን ያለፈና የወደፊት አኗኗራቸውን፣ ያለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ፣ በአጠቃላይ ስለ ህይወት ያላቸውን ፍልስፍና ለመግለፅ እንደሚጠቀሙባቸው በጥናቱ ተረጋግጧል፡፡

Description

Keywords

የስራ ቃል ግጥሞች ክዋኔና

Citation