የቃላት መማር ብልሃቶችን በግልጽ ማሰልጠን ለሁለተኛ ቋንቋ ተማሪዎች የቃላት ችሎታ መዳበር ያለው አስተዋጽኦ፤ ጾታ ተኮር ሙከራዊ ጥናት (በዘጠነኛ ክፍል ኦሮምኛ ቋንቋ አፍፈት ተማሪዎች) ተተኳሪነት
No Thumbnail Available
Date
2010-06
Authors
Journal Title
Journal ISSN
Volume Title
Publisher
Addis Ababa University
Abstract
የዚህ ጥናት አብይ ዓላማ በኦሮምኛ ቋንቋ አፋቸውን የፈቱ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪዎች በአማርኛ ቋንቋ ትምህርት የቃላት መማር ብልሃቶችን በግልጽ መሰልጠናቸው የቃላት ችሎታቸውን ለማዳበር ያለውን አስተዋጽኦ በከፊል ፍትነታዊ ምርምር መፈተሸ ነበር፡፡ ይህን ዓላማ ለማሳካትም በዱከም ከተማ የሚገኘው የኦዳ ነቤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአመቺ ናሙና ተመርጧል፡፡ በትምህርት ቤቱ ከሚገኙት አስራ ሁለት የዘጠነኛ ክፍል የመማሪያ ክፍሎች የሁለት ክፍል ተማሪዎች በቀላል የእጣ ናሙና ተመርጠዋል፡፡ በመሆኑም የሙከራው ቡድን ተማሪዎች የቃላት መማር ብልሃቶች ስልጠና እየተሰጣቸው፣ የቁጥጥር ቡድኑ ተማሪዎች ደግሞ በተለመደው የቃላት ትምህርት አቀራረብ የቃላት ትምህርትን በአስራ አራት ሳምንታት ለ28 ክፍለ ጊዜያት እንዲማሩ ተደርጓል፡፡ መረጃዎቹ በቃላት ፈተናና በቃላት መማር ብልሃቶች አጠቃቀም መለኪያ የጽሑፍ መጠይቅ በቅድመትምህርትና በድህረትምህርት ተሰብስበዋል፡፡ በቃላት ፈተናና በቃላት መማር ብልሃቶች አጠቃቀም የጽሑፍ መጠይቅ የተሰበሰቡት መረጃዎች በየአይነታቸው ከተደራጁ በኋላ በገላጭና በድምዳሜያዊ ስታትስቲክስ (የነጻ ናሙናዎች ቲ-ቴስት፣ ዳግም ልኬት ናሙናዎች ቲ-ቴስትና በፒርሰን ፕሮዳክት ሞመንት የተዛምዶ መለኪያ) ተተንትነዋል፡፡ በውጤት ትንተናው መሰረትም የሙከራው ቡድን ድህረትምህርት የቃላት ፈተና አማካይ ውጤት ከቁጥጥሩ ቡድኑ የቃላት ፈተና አማካይ ውጤት በልጦ ጉልህ ልዩነት (p=0.000) አሳይቷል፡፡ በተመሳሳይ የሙከራው ቡድን የድህረትምህርቱ የቃላት መማር ብልሃቶች አጠቃቀም መለኪያ የጽሑፍ መጠይቅ አማካይ ውጤት ከቅድመትምህርቱ የቃላት መማር ብልሃቶች አጠቃቀም አማካይ ውጤት በልጦ ጉልህ ልዩነት (p=0.002) አሳይቷል፡፡ እንዲሁም በሙከራው ቡድን ሴትና ወንድ ተማሪዎች ድህረትምህርት የቃላት ፈተና አማካይ ውጤት መካከል ጉልህ ልዩነት አለመኖሩን (p=.959) አሳይቷል፡፡ ከዚህም ባሻገር በሙከራው ቡድን ድህረትምህርት የቃላት መማር ብልሃቶች አጠቃቀም አማካይ ውጤትና በድህረትምህርቱ የቃላት ፈተና አማካይ ውጤት መካከል በጣም ጠንካራ ጉልህ ተዛምዶ መኖሩን (r=.947, p= .000)ጥናቱ አመልክቷል፡፡ ከጥናቱ ግኝቶች በመነሳትም የቃላት መማር ብልሃቶችን በውህደት በግልጽ ማሰልጠን የተማሪዎችን የቃላት ችሎታ፣ የብልሃት ግንዛቤና አጠቃቀም፣ በሴትና ወንድ ተማሪዎች መካከል የነበረውን የቃላት ችሎታ ልዩነት በማጥበብ በተመጣጣኝ ደረጃ ችሎታቸውን ለማሳደግ ከተለመደው የቃላት ማስተማሪያ ዘዴ የበለጠ አስተዋጽኦ አለው ከሚል መደምደሚያ ላይ ተደርሷል፡፡ ከዚህም ሌላ ብልሃቶችን በግልጽ ማሰልጠን የብልሃት አጠቃቀምንና የቃላት ችሎታን ለማዛመድ አወንታዊ አስተዋጽኦ አለው ወደሚል መደምደሚያ ተደርሷል፡፡ ከጥናቱ ግኝቶች በመነሳትም ስነትምህርታዊ የመፍትሄ ሀሳቦች ተጠቁመዋል፤ የወደፊት የምርምር አቅጣጫዎችም ተመላክተዋል፡፡
Description
Keywords
በኦሮምኛ ቋንቋ አፋቸውን የፈቱ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪዎች በአማርኛ ቋንቋ ትምህርት