የባህል ሕክምና ዕውቀት እና የሥነ ምህዳር ዐውዳዊ መስተጋብር ትንተና በደቡብ ጎንደር ዞን ማኅበረሰብ
No Thumbnail Available
Date
2012-07
Authors
Journal Title
Journal ISSN
Volume Title
Publisher
አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ
Abstract
ይህ ጥናት “የባህል ሕክምና ዕውቀት እና የሥነ ምህዳር ዐውዳዊ መስተጋብር ትንተና በደቡብ ጎንደር
ዞን ማኅበረሰብ” በሚል ርዕስ የቀረበ ሲሆን፤ የጥናቱ ዐበይት ጥያቄዎች፤ የባህል ሕክምና ዕውቀትና
ትግበራ በምን ዓይነት የሥነ ምህዳር ዐውድ ላይ ተመስርቶ ይከወናል? የዕውቀቱ ማሕቀፍ እስከ ምን
ይደርሳል? የሚሉ ይዘቶችን በማንሳት ለመፈተሽ የታለመ ነው፡፡ የምርምሩ ዐቢይ ዓላማ በደቡብ ጎንደር
ዞን ማኅበረሰብ የሚካሄደውን፤ የባህል ሕክምና ዕውቀት እና የሥነ ምህዳር ዐውዳዊ መስተጋብርን
መመርመር ነው። ጥናቱ፤ የሕመም መንስኤ እሳቤን መግለጽ፤ የበሽታ መለያና መመርመሪያ ዘዴዎችን
ማብራራት፤ የባህል መድኃኒት ቅመማና አሰጣጥ ሥርዓት ዐውዳዊ ክዋኔን መተንተን፤ የባህል ሕክምና
ዕውቀት ለሥነ ምህዳር ጥበቃ ያለውን አስተዋጽኦ መለየት የሚሉ ዝርዝር ዓላማዎችን አካቷል፡፡
እነዚህን ዝርዝር ዓላማዎች ከግብ ለማድረስ የመስክ መረጃዎች፤ በቃለመጠይቅ፣ በምልከታ፣ በቡድን
ተኮር ውይይት እና በንጥል ጥናት ዘዴዎች ተሰብስበው፤ በማስታወሻ፣ በመቅረጸ ድምጽ፣ በፎቶና
በቪዲዮ ካሜራ ተሰንደዋል፡፡ የመስክ መረጃ ሰጪዎች፤ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችን ብቻ ታላሚ
በማድረግ (ከሶስት ወረዳዎች 76 ሰዎች) በዓላማ ተኮር እና በአጋዥ ጠቋሚ ናሙና ስልት ተመርጠዋል፡፡
ከዐብይና አጋዥ መረጃ ሰጪዎች የተሰበሰቡ መረጃዎች፤ በይዘትና በምድብ ተደራጅተው፤ ዓይነታዊ
የምርምር ይዘትን በመከተል በሥነ ዕውቀት እና በማኅበራዊ ግንባታ፣ በዐውድ-ተኮር ክዋኔ እና ሕዝባዊ
የሕመም መንስኤ ንድፈ ሃሳቦችን መሰረት በማድረግ፤ ከዐውድ-ተኮር ክዋኔ፣ ከተፈጥሮ ባሕርይ እና
ከባህል-ተኮር ማብራሪያ ሞዴሎች አንፃር በመፈተሽ፤ በገላጭ፣ በይዘት ትንተና እና ትርጓሜ
(Interpretation) ስልት ተተንትነው ቀርበዋል፡፡ በትንታኔው መሰረት በደቡብ ጎንደር ዞን ማኅበረሰብ
/በባህል ሐኪሞች/ እሳቤ፤ የሕመም መንስኤዎች ጅን፣ ዛር፣ ቡዳ፣ የመሬት እና የዐየር ጋኔል ተደርገው
እንደሚታሰቡ፤ በጥናቱ ተረጋግጧል፡፡ እነዚህ የባህል ሐኪሞች ዓለማዊና መንፈሳዊ የምርመራ
ዘዴዎችን በመተግበር፤ የጤና ኃይል ሚዛን ማስተካከያ ባሕርያትን (ነፋስ፣ እሳት፣ ዉኃና መሬት)
በመከተል እና የበሽታ ባሕርይ ምድቦችን በማጤን ድንገተኛና አጣዳፊ፣ ቆንጣጭና ሰርሳሪ፣ አቃጣይና
አስለፍላፊ፣ አብራጅና አድካሚ፣ አንቀጥቃጭና አርገብጋቢ፣ አደንዛዥ እና አወፋሪ በማለት፤ አካልን
የሚያደቁ (ለቁስል) እና መንፈስን የሚያስጨንቁ የሕመም ዓይነቶችን እንደሚፈውሱ፤ ጥናቱ ጠቁሟል፡፡
የባህል መድኃኒት ቅመማና አሰጣጥ ሥርዓት ዐውዳዊ ክዋኔ፤ ከባህል መድኃኒት ግብዓት አሰባሰብ እስከ
መድኃኒት አሰጣጥ ድረስ ሲተገበር፤ በሥርዓተ ገቢር እና በፀሎት የሚመራ፣ በዐውድ (በቀን፣ በሠዓት፣
በጊዜ፣ በቦታና በሁነት) የተወሰነ፣ በድርጊት የታጀበና የተገደበ፣ ብላ/ አትብላ፣ አድርግ/ አታድርግ
መመሪያና ገደቦችን በመከተል ይፈፀማል፡፡ የመድኃኒት ቅመማ ሂደቱም፤ በማጠብ፣ በማድረቅ፣
በመልቀም፣ በመከትከት፣ በመጨቅጨቅ፣ በመውቀጥ፣ በመፍጨት፣ በመንፋት፣ በመቀቀል፣ በማንጠርና
በማሸግ ወደ መድኃኒት አሰጣጥ ይሸጋገራል፡፡ የመድኃኒት አሰጣጥ ሥርዓቱም፤ በሚጠጣ፣ በሚሸተት፣
በሚታጠን፣ በሚጨስ፣ በሚቀባና በሚቀበር ይዘት እንደሚከወን፤ ጥናቱ አረጋግጧል፡፡ በመጨረሻም
የባህል ሐኪሞች እምነት፣ ዕውቀትና ተግባር ለዕፅዋትና እንስሳት ጥበቃ በማድረግ፤ በአድባራት፣
በገዳማት፣ በፀበልና በደብር ቦታዎች የመትከል፣ የመዝራትና የማባዛት ልማድ መኖር ለአካባቢ ሥነ
ምህዳር ጥበቃ አበርክቶ ሲያደርግ፤ የዕፅዋትና የእንስሳት ንግድ፣ የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የከተማ
መስፋፋት፤ ለዕፅዋትና እንስሳት መጥፋትና መሰደድ፣ ለሥነ ምህዳር ሚዛን መዛባት መንስኤ
መሆናቸውን ጥናቱ አመላክቷል፡፡ ይህን ጉዳይ ታሳቢ በማድረግ፤ የባህል ሕክምና ዕውቀትን ከሥነ
ምህዳር ይዘት ጋር በማስተሳሰር፤ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ የልማት ድርጅቶች፣ የአካባቢው
ማኅበረሰብና አመራር አካላት፤ በርዕሰ ጉዳዩ ዙሪያ ቢወያዩና የጋራ መፍትሔ ቢፈልጉ መልካም ነው፡፡
Description
Keywords
የባህል ሕክምና ዕውቀት እና የሥነ ምህዳር ዐውዳዊ መስተጋብር ትንተና