የመጻፍ ክሂል ይዘቶች አደረጃጀት ትንተና (በዘጠነኛ እና በአስረኛ ክፍሎች የአማርኛ ቋንቋ መማሪያ ተተኳሪነት)
No Thumbnail Available
Date
2024-06
Authors
Journal Title
Journal ISSN
Volume Title
Publisher
አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ
Abstract
የዚህ ጥናት ዋና ዓላማ በዘጠነኛና በአስረኛ ክፍሎች የአማርኛ ቋንቋ መማሪያ መጻሕፍት ውስጥ ያሉ የመጻፍ ክሂል ይዘቶችና የትምህርት ልምዶች የተደራጁበትን መንገድ መፈተሸ ነው፡፡ ለዚህም ጥናቱ አይነታዊ ምርምርን ተግባራዊ አድርጓል፡፡ አደረጃጀቱን በተከታታይነት ስር ተደጋግመው የመጡ ይዘቶች ያላቸውን የድግግሞሽ መጠንና የድግግሞሻቸውን ተገቢነት፣ በተለጣጣቂነት ስር ከቅርብ ወደሩቅ፣ ከቀላል ወደከባድ፣ ከተጨባጭ ወደረቂቅ እና ከቀድሞ መጥ አንጻር እንዴት እንደተደራጁና ከውህደት አንጻር ደግሞ የመጻፍ ክሂል ይዘቶችና የትምህርት ልምዶች ከሌሎች ትምህርቶች ጋር መደራጀት አለመደራጀቱ ተፈትሿል፡፡ የሰነድ ፍተሻ የተነሱትን ጉዳዮች ለማጥናት በመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴነት አገልግሏል፡፡ በሰነድ ፍተሻ የተገኘው መረጃ በብዛት በአይነት በአይነት በመሰብሰቡ ለመረጃ መሰብሰቢያነት ያገለገለው የመረጃ መተንተኛ ስልት በአመዛኙ አይነታዊ የመረጃ መተንተኛ ስልት ነው፡፡ ጥቂት የቁጥር መረጃዎች ስላሉ፣ ቀላል የድምርና የመቶኛ ስሌቶች በትንተናው ውስጥ ስላገለገሉ በተወሰነ ደረጃ መጠናዊ የመረጃ መተንተኛ ስልትም በጥናቱ ውስጥ አገልግሏል፡፡ በመሆኑም አተናተኑ ቅይጥ ስልትን የተከተለ ነው፡፡ የጥናቱ ውጤትም የሚያሳየው በመጻሕፍቱ ውስጥ የተካተቱ ይዘቶችና የትምህርት ልምዶች ተከታታይነታቸውና ተለጣጣቂነታቸው በተገቢውና ንድፈሀሳቡ ላይ በሰፈሩት መልኩ እንዳልቀረቡ ጥናቱ አሳይቷል፡፡ ተተኳሪ ይዘቶችና የትምህርት ልምዶች ተደጋግመው የቀረቡበት መጠን በቂ እንዳልሆነና ተማሪዎችንም የመጻፍ ክሂልን ለማለማመድ ብቁ እንዳልሆኑ በትንተናው ታይቷል፡፡ በተመሳሳይ ሁለቱም መጻህፍት ውስጥ የተካተቱ ይዘቶችና የትምህርት ልምዶች ከቀላል ወደከባድ፣ ከተጨባጭ ወደረቂቅና ከቀድሞ መጥ አንጻር ከመደራጀት አንጻር በከፊል ጠንካራ ጎን ያላቸው ሲሆን በከፊል ደግሞ ድክመት ታይቶባቸዋል፡፡ ከቅርብ ወደሩቅ ያላቸው አደረጃጀት ግን ጠንካራ ጎኑ እንደሚያመዝን በጥናቱ ተረጋግጧል፡፡ በመሆኑም የይዘቶችና የትምህርት ልምዶች ተከታታይነትና ተለጣጣቂነት በአብዛኛው ድክመቱ እንደሚያመዝን የጥናቱ ግኝት አሳይቷል፡፡ ውህደቱን በተመለከተ ግን ጥሩ የሚባል አደረጃጀት እንዳለ የትንተናው ውጤት አመልክቷል፡፡ የመጻፍ ክሂል ትምህርት ሲደራጅ ከሌሎች የትምህርት ይዘቶች ጋርም የጎን ለጎን ግንኙነት እንዲኖራቸውና ተዋህደው እንዲደራጁ የተደረገ በመሆኑ ውህደቱ የሰመረ ነው፡፡ ከዚህ ግኝት በመነሳትም አጥኚው የመጻፍ ክሂል ይዘቶችና የትምህርት ልምዶች ሲደራጁ በበቂ መጠን ተደጋግመው እንዲደራጁ፣ ተደጋግመው የመጡ ይዘቶችም ከቀላል ወደከባድ፣ ከተጨባጭ ወደረቂቅ፣ ከቅርብ ወደሩቅ እንዲሁም አስፈላጊነታቸውን ታሳቢ በማድረግ እንዲደራጁ፣ መማሪያ መጻህፍት አዘጋጆችና አስማሚዎች በመጽሐፍ ዝግጅት ወቅት፣ መምህራንም ትምህርቱን ክፍል ውስጥ በሚያቀርቡበት ወቅት የአደረጃጀት መርሁን ታሳቢ እንዲያደርጉ የመፍትሄ ሀሳቦችን ሰንዝሯል፡፡