ዋልተንጉሥ መኮንን (ዶ/ር)ደስታ አማረ (ዶ/ር)ሥራዬ እንዳለው ውበቴ2024-10-032024-10-032016-07https://etd.aau.edu.et/handle/123456789/3491ይህ ጥናት “ሊሚናሊቲ እና ለውጥ በሕይወት ሽግግር ሥርዓቶች በጃቢ ጠህናን ወረዳ ማኅበረሰብ” በሚል ርዕስ ተካሂዷል፡፡ በዋናነት ሊሚናሊቲንና ለውጥን ከሕይወት ሽግግር (ወሊድ፣ ጋብቻና ሞት) ሥርዓተ ክዋኔዎች ጋር አያይዞ አጥንቷል፡፡ የሕይወት ሽግግሮች በአንድ በኩል የግለሰብ በሌላ በኩል የጋራ ጉዳዮች በመሆናቸው ከሽግግሮች ባሕርይና ከማኅበረሰቡ ባህል ጋር በተያያዙ ምክንያቶች አስጊና አሳሳቢ፣ ባለጉዳዮችንም ለልዩ ልዩ ለውጦች የሚያጋልጡ ናቸው፡፡ በመሆኑም በሕይወት ሽግግሮች ወቅት የተለያዩ ሥርዓተ ክዋኔዎች ይፈጸማሉ፡፡ ጥናቱ እነዚህን ሥርዓተ ክዋኔዎች ሽግግሩን ከሚያካሂዱ ባለጉዳዮች ጋር በማስተሳሰር፣ በዐማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፣ በምዕራብ ጎጃም ዞን፣ በጃቢ ጠህናን ወረዳ የኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት ተከታይ ማኅበረሰብ እምነትና ባህል ማሳያነት አጥንቷል፡፡ የሕይወት ሽግግሮች ባለጉዳይን አስጨናቂ ያደረጉባቸውን ሁኔታዎች መለየት፤ በወቅቱ የሚከወኑ ሥርዓቶችን ዓላማ መግለጽ፤ ሽግግሩ ያስከተላቸውን ለውጦች መፈተሽ፣ በሽግግሩ ከተገኙ ለውጦች ጋር የሚያስተዋውቁ ወይም የሚያላምዱ ብልሃቶችን መመርመር እና በሕይወት ሽግግር ሥርዓቶች ላይ የተገለጡ የጋራ ትዕምርቶችን መተንተን የሚሉ ዓላማዎችን አሳክቷል፡፡ ጥናቱ ዓይነታዊ ሲሆን መረጃዎች ከቀዳማይና ከካልዓይ ምንጮች ተሰብስበዋል፡፡ ምልከታ፣ ቃለ መጠይቅ እና ተተኳሪ የቡድን ውይይት መረጃዎች የተሰበሰቡባቸው ዘዴዎች ሲሆኑ በሂደት አራት ዙር የመስክ ሥራ ተከናውኗል፡፡ በወረዳው ከሚገኙ አርባ አንድ ቀበሌዎች ውስጥ በዓላማ ተኮር የናሙና አመራረጥ ስልት ሥድስት ቀበሌዎች ተጠኝ ሆነው ተመርጠዋል፡፡ ለጥናቱ መረጃ በመስጠት ሠላሳ አምስት ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን ከእነዚህ መካከል አስራ አራቱ በቁልፍ መረጃ ሰጪነት ተሳትፈዋል፡፡ አመራረጡም ጾታን፣ ማኅበራዊ ደረጃን፣ እድሜን፣ ለጉዳዩ ያለን ተጋላጭነት እና ሀሳብን የመግለጽ ብቃት ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው፡፡ መረጃው በዲጅታል ካሜራ፣ በመቅረጸ ድምጽ እና በማስታወሻ ደብተር ተይዟል፡፡ ትክክለኛነቱም መረጃ ሰጪዎች በተደጋጋሚ ያነሷቸው፣ በምልከታ ወቅት ያጋጠሙ እና በተተኳሪ የቡድን ውይይት ወቅት ተወያይተው የተስማሙባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን በመለየት ተመሳክሯል፡፡ ከመረጃ ሰጭዎች የተገኙ መረጃዎች ትዕምርታዊ መስተጋብር፣ ተግባራዊ መዋቅራዊ እና ፍካሬ ልቡናዊ ንድፈ ሀሳቦች እንደ አስፈላጊነታቸው ለትንታኔ ማሕቀፍነት ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡ የመረጃ ትንተናው እንደሚያሳየው የጃቢ ጠህናን ወረዳ ማኅበረሰብ ከሃይማኖቱ፣ ከእምነቱ እና ከባህሉ የወጡ በርካታ ባህላዊ እሴቶች ባለቤት ነው፡፡ የሰውን ልጅ ስጋዊ አፈጣጠርና ባሕርይ ከመሬት አፈጣጠር ጋር፤ መንፈሳዊ አፈጣጠሩን ደግሞ ከነፋስ፣ ከእሳት ከውሃ እና ከመሬት ባሕርያት ጋር ያዛምዳል፡፡ በሌላ በኩል የሰው ልጅ ልባዊት (ሀሳብ)፣ ነባቢት (ንግግር) እና ህያዊት (ዘላለማዊነት/ትንሳኤ)፣ የተባሉ የመንፈሳዊ ሰብዕና መገለጫዎች ወይም ባሕርያተ ነፍስ አሉት ብሎ ያምናል፡፡ የጃቢ ጠህናን ወረዳ ማኅበረሰብ እርስ በእርሱ እንዲተሳሰርና እንደ ማኅበረሰብ እንዲቀጥል ያስቻሉ የተለያዩ የዝምድና መፍጠሪያ እና አብሮ የመኖር ብልሃቶች አሉት፡፡ የሕይወት ሽግግሮች ባለጉዳዩን የደረጃ ሽግግር እና ለውጥ እንዲያካሂድ የሚያደርጉ መሆናቸው፤ ከሽግግሮች ጸባይ እና ከማኅበረሰቡ ባህል በሚነሱ ምክንያቶች ዋናው የሽግግር ወቅት አስጊ እና አሳሳቢ መሆኑን አሳይቷል፡፡ ከዚህም የተነሳ የሕይወት ሽግግሮች አዲስ እና መለማመጃ የሌላቸው፣ ድንገት ደራሽ፣ ቅጽበታዊ፣ ምሥጢራዊ፣ ራሳቸውን የማይደግሙ፣ አስገዳጅ እና ነጣይ በመሆናቸው ባለጉዳዮችንም ሆነ ማኅበረሰቡን ለጭንቀትና ለግራ መጋባት ይዳርጋሉ፡፡ በወቅቱ የተፈጠረን ጭንቀት እና ግራ መጋባት ለመቀነስ ወይም ለማከም የተለያየ ዓላማና ሚና ያላቸው ሥርዓተ ክዋኔዎች ከቅድመ ሽግግሩ ጀምሮ ዋናው ሽግግር ከተካሄደ በኋላም ይፈጸማሉ፡፡ የሕይወት ሽግግሮች ባለጉዳዮች የስም፣ የአለባበስና የአጊያጊያጥ፣ የቋንቋ አጠቃቀም፣ የማኅበራዊ ደረጃና የስነ ልቡና ለውጥ የሚያካሂዱባቸው መሆናቸውን እና ከእነዚህ ለውጦች ጋር የሚያስተዋውቁ እና የሚያለማምዱ ክዋኔዎችን አሳይቷል፡፡ በሕይወት ሽግግር ሥርዓቶች ወቅት ከተገለጡ የጋራ ትዕምርቶች መካከል ቀዳሚን ማክበር፣ ጀግናን ማወደስ፣ ሃይማኖትን፣ ሀገርን እና ሥራን መውደድ፣ መልካም ምግባር ማኅበረሰቡ በተለመደው መልክ እንዲቀጥል ያገዙ ዋና ዋና መልካም እሴቶች ናቸው፡፡amሊሚናሊቲ፣ ለውጥ፣ ሥርዓተ ክዋኔ፣ የሕይወት ሽግግሮች፣ ትዕምርታዊ መስተጋብር ንድፈ ሀሳብ፣ ተግባራዊ መዋቅራዊ ንድፈ ሀሳብ፣ ፍካሬ ልቡናዊ ንድፈ ሀሳብ፣ ጃቢ ጠህናን ወረዳ“ሊሚናሊቲ” እና ለውጥ በሕይወት ሽግግር ሥርዓቶች በጃቢ ጠህናን ማኅበረሰብThesis